Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ የተቀናጀ ጥረት እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ የተቀናጀ ጥረት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አቶ ደመቀ ከ78ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን በአየር ንብረት ለውጥ እና መወሰድ ባለባቸው የመከላከያ ተግባራት ዙሪያ ባተኮረ መድረክ ላይ ተሳትፈዋል፡፡

በዚህ ወቅትም በኢትዮጵያ የአየር ንበረት ለውጥን ለመቋቋም በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 32 ቢሊየን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መተከላቸውን አንስተዋል፡፡

እየተባባሰ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ለመቋቋምም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በጉዳዩ ላይ በትብብር መስራት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በተመሳሳይ ከ78ኛው ከተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዚዳንት ዳኒስ ፍራንሲስ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የመከሩት አተ ደመቀ፤ ኢትዮጵያ የዘላቂ ልማት ግቦችን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመተግበር ቁርጠኛ መሆኗን አስገንዝበዋል፡፡

ዳኒስ ፍራንሲስ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የምታደርገውን ጥረት አድንቀው÷ ተቋማቸው ለግቦቹ ስኬት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

በተጨማሪም አቶ ደመቀ ከተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) ዳይሬክተር ጀነራል ገርድ ሙለር ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱም ዩኒዶ በኢትዮጵያ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ዳሬክተሩ ጀነራል ገርድ ሙለር አረጋግጠዋል፡፡

ዩኒዶ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ዘርፈ ብዙ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚፈልግ መግለጻቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.