Fana: At a Speed of Life!

የቅዳሜና የእሁድ ገበያ በአዘቦት ቀናትም እንዲካሄድ ተጠየቀ

 

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የኑሮ ውድነት ለማቃለል ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል አንዱ የሆነው የቅዳሜና የእሁድ ገበያ በአዘቦት ቀናትም እንዲካሄድ ተጠየቀ።

የገበያ ሁኔታን በተመለከተ አስተያየታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የሰጡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የኑሮ ውድነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ኑሯቸውን ፈታኝ እያደረገው እንደሆነ ጠቁመዋል።

የምግብ ነክ እና የሸቀጣሸቀጦች ዋጋ መናር ከሚያገኙት ገቢ ጋር የማይመጣጠን መሆኑንም ነው የገለፁት፡፡

በተለይ በመንግስት ስራ የሚተዳደሩ (በአነስተኛ ገቢ የሚተዳደሩ)፣ በቤት ኪራይ ለሚኖሩ እና ልጆች ያላቸው እንዲሁም ልጆቻቸውን በክፍያ ለሚስተምሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጫናው ይበልጥ እንደሚበረታም ነው የያነሱት፡፡

መንግስት የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ እና ገበያውን ለማረጋጋት ለማሕበረሰቡ ተደራሽ የሆኑ የመገበያያ ስፍራዎችን በማዘጋጀት ሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎቱን እንዲያገኝ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ይህ ተግባር መልካም እንደሆነ አንስተው የገበያ ቀናቱ በቅዳሜና እሁድ ብቻ መወሰን እንደሌለበት ገልጸው፤ በአዘቦት ቀናትም እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የቅዳሜ እና የእሁድ የገበያ ማዕከሎች በአዘቦት ቀናትም እንዲሰሩ ከማድረግ ባሻገር ቁጥጥር እንደሚያስፈልጋቸው አስተያየት ሰጪዎቹ አክለዋል፡፡

እንዲሁም እህል (በተለይ እንደ ጤፍ በቆሎ፣ ስንዴ ያሉ)ምርቶች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ በስፋት ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ቢቀርብ የኑሮ ውድነቱን እንደሚያረጋጋው ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡

እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መረጃ በሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራት፣ የሰብልና የአትክልት አቅራቢዎች፣ የጅምላ ነጋዴዎች፣ በምግብ ማቀነባበርያ የተሰማሩ ፋብሪካዎችና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የሚገኙ የህብረት ስራ ማህበራትን በማሳተፍ በየሳምንቱ የእሁድ ገበያን በከተማዋ በተመረጡ 96 ቦታዎች ማቅረብ ተችሏል፡፡

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.