በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ህዝቡ የድርሻውን መወጣት አለበት – ሜጀር ጄኔራል ሙሉዓለም አድማሱ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደመራ፣ መስቀልና መውሊድን ጨምሮ ሌሎችም ሃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ህዝቡ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት የባህር ዳርና አካባቢው ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሜጀር ጄኔራል ሙሉዓለም አድማሱ ገለጹ።
ኮማንድ ፖስቱ እና የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር በዘላቂ ሰላም ማስከበር ዙሪያ በባህርዳር ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።
ሜጀር ጄኔራል ሙሉዓለም በዚሁ ጊዜ÷ በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰtው የፀጥታ ችግር ከደረሰው ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ባሻገር በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎች ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል።
አያይዘውም መንግሥት ሰላምን ለማስፈን እና የህግ የበላይነትን ለማስከበር ከህዝቡ ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
የዘመን መለወጫ በዓልን በሰላም ማክበር መቻሉን ጠቅሰው ለዚህም የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጥረት ብቻ ሳይሆን ህዝቡም ሰላም ፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በቀጣይም ሕዝቡ የመስቀልና የመውሊድ በዓልን ጨምሮ ሌሎች ሃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላትን በሰላም እንዲያከብር የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የፀጥታ አካላት በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አስሜ ብርሌ በበኩላቸው፥ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ሰላምና ህግን ለማስከበር ሌት ተቀን እየሰራ ካለው የፀጥታ ኃይሉ ጎን ሊቆም እንደሚገባ ተናግረዋል።