ያሆዴ ባህላዊና ታሪካዊ የስልጣኔ ማሳያ ነው – አቶ ቀጀላ መርዳሳ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)ያሆዴ ባህላዊና ታሪካዊ የሆነ የሀዲያን ማህበረሰብ ቀደምት ስልጣኔ የሚያሳይ ነው ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ ተናገሩ።
የሀዲያ የዘመን መለወጫ የሆነው ያሆዴ በአል የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ፣የሀዲያ ዞን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እቴነሽ ሙሉጌታ ፣የዞኑ አመራሮች፣የሃገር ሽማግሌዎች እና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው።
በመርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ÷ያሆዴ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እሴቶችን አቅፎ መያዙን ገልፀው ለበአሉ እድገት እንሰራለን ብለዋል።
ቀጣዩ ዘመንም የፍቅር ፣የደስታ፣ የሰላም፣ እና የብልፅግና እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አብርሀም መጫ÷ይህንን ኢትዮጵያዊ እሴት በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ጥረቶች መቀጠላቸውን ተናግረው ለዚህም ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
በቃለአብ ግርማ