ብራዘርስ ጋዝ ኩባንያ በኢትዮጵያ የመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ገለፀ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኡም አልኩዌን ኤምሬት የሚገኘው ብራዘርስ ጋዝ (BROTHERS GAS) ኩባንያ በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋዩን የማፍሰስ ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ፡፡
በዱባይና ሰሜን ኤምሬቶች የኢትዮጵያ ቆንስል ጄኔራል አምባሳደር አክሊሉ ከበደ ኩባንያውን የጎበኙ ሲሆን÷ ከኩባያው ሥራ አስኪያጅ ሙሃመድ ፋርሃን ማሊክ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱም÷ አምባሳደር አክሊሉ በኢትዮጵያ ባለው ዕምቅ የኢንቨስትመንት አማራጮችና በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ቅድሚያ በተሰጠው የማዕድን፣ ተፈጥሮ ጋዝና ነዳጅ መስክ ያለውን የመንግስት ፖሊሲ በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል፡፡
የኩባንያው ስራ አስኪያጁ ሙሃመድ ፋርሃን በበኩላቸው÷ ኩባንያቸው በመስኩ ያለውን እምቅ ልምድና በኢትዮጵያ ያለውን ዕድል ለመጠቀም ኩባንያቸው በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋዩን የማፍሰስ ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል፡፡
በዚህም በቅርቡ ኩባንያው በኢትዮጵያ የቅድመ-ኢንቨስትመንት ጉብኝት ለማድረግ ልኡክ ለመላክ እቅድ እንዳለው መግለፃቸውን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
አምባሳደር አክሊሉ÷ ኩባንያው በኢትዮጵያ ለሚያደርገው ኢንቨስትመንት መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል፡፡
ብራዘርስ ጋዝ ኩባንያ እ.ኤ.አ. በ1992 የተመሰረተ ሲሆን ለንግድ፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ ኢንዱስትሪና ቤት ግብአት የሚሆኑ ምርቶች በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በእስያና በአሜሪካ ገበያ የሚያቀርብ ግዙፍ ኩባንያ ነው፡፡