የአውሮፓ ኮሚሽን የ127 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ ለቱኒዚያ ፈቀደ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአውሮፓ ኅብረት እና በቱኒዚያ መካከል የተፈረመውን የመግባቢያ ሠነድ ተግባራዊ ለማድረግ የአውሮፓ ኮሚሽን የ127 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ መፍቀዱን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ ከፈቀደው ጠቅላላ ገንዘብ 60 ሚሊየን ዩሮው ለሀገሪቷ በጀት ድጋፍ የሚውል ሲሆን 67 ሚሊየን ዩሮው ደግሞ ተፈናቃዮችን ለመደገፍ የሚውል መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
በሚቀጥለው ሣምንት ውስጥ የኮሚሽኑ ባለሥልጣናት ልዑካን ቡድን ቱኒዚያን ከጎበኙ በኋላ በተፈረመው የመግባቢያ ሠነድ መሠረት ገንዘቡ የሚለቀቅበት ሁኔታ ይመቻቻል ተብሏል፡፡
ባለሥልጣናቱ ቱኒዚያ የሚሄዱትም ቅድሚያ በሚሰጣቸው ተግባራት ላይ ሊወያዩ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ቱኒዚያ ÷ በምጣኔ ሐብት ቀውስ ፣ በሥራ አጥነት ፣ በኑሮ ውድነት እና ወደ አውሮፓ መሻገር በሚፈልጉ ፍልሰተኞች የተወጠረች ሰሜን አፍሪካዊት ሀገር ናት፡፡