ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ለሆኑ ሰዎች የኮሌራ በሽታ መከላከያ ክትባት ተሰጠ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮሌራ በሽታን ለመከላከል በተካሄደ የክትባት ዘመቻ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ሰዎች መከተባቸውን የአማራ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የተከሰተውን የኮሌራ በሽታ ለመከላከል ከመስከረም 5 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የባህር ዳር እና ጎንደር ከተሞችን ጨምሮ ተጋላጭ በሆኑ ዘጠኝ ወረዳዎች ክትባቱ መሰጠቱ ተገልጿል፡፡
በኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር አብረሃም አምሳሉ ለኢዜአ እንደገለጹት÷ ኮሌራን ለመከላከል ክትባት አንዱ መንገድ ቢሆንም የበሽታው ብቸኛ የመከላከያ መንገድ ስላልሆነ ሕብረተሰቡ የግልና የአካባቢ ንጽህናን ሊጠብቅ ይገባል፡፡
በክልሉ 4 ሺህ 41 ሰዎች በኮሌራ በሽታ ቢያዙም በተደረገላቸው የሕክምና ክትትል 3 ሺህ 916ቱ ጤናቸው ተመልሶ ወደመደበኛ ሕይወት መመለሳቸውም ተገልጿል፡፡