በአማራ ክልል ከቱሪዝም ዘርፍ ከ7 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ እንደሚገኝ ይጠበቃል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በዘንድሮው የበጀት ዓመት ከቱሪዝም ሀብት ዘርፍ ከ7 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
በቢሮው የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር አቶ መልካሙ አደም እንደገለጹት÷ በዓለም ቅርስነት የሚታወቁት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የጎንደር አብያተ መንግስትታትና የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክን ጨምሮ ሌሎችም በክልሉ የሚገኙ ቅርሶች የጎብኚ መዳረሻ መሆናቸውን አመላክተዋል።
በበጀት ዓመቱ እነዚህን የመስህብ ስፍራዎች ከ21 ሚሊየን በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች እንደሚጎበኙና ከዘርፉም ከ7 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የተናገሩት።
ለዚህም በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች የመስህብ ሃብቶችን ማስተዋወቅ፣ የመስህብ ስፍራ መሰረተ ልማትን ማስፋፋትና የአስጎብኚዎችን አቅም ማሳደግ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ እንደሆነ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የቱሪዝም ዘርፍ በተለይ ሰላምን አጥብቆ እንደሚሻ የጠቀሱት አቶ መልካሙ፥ የቱሪዝም ዘርፉን ይበልጥ ለማነቃቃት ሰላም ማስጠበቅ ላይ ተባብሮ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
የክልሉ ህዝብ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፎውን በማጎልበት የዘርፉን ልማት ለማጠናከር የበኩሉን መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል።