በቀጣዮቹ 10 ቀናት አብዛኛዎቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች ዝናባማ ይሆናሉ – ኢንስቲትዩቱ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚቀጥሉት 10 ቀናት ዝናብ ሰጭ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በአብዛኛው የደቡብና ደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች የተሻለ ገጽታ እንደሚኖራቸውን የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
ቀደም ብሎ የጀመረው የክረምት ወቅት ዝናብ በምዕራብ አጋማሽ የሚቀጥል ሲሆን÷ ወደ ደቡብና ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ እንደሚስፋፋም ተገልጿል፡፡
በሚቀጥሉት 10 ቀናት ሁሉም የወለጋ ዞኖች፣ ጅማ፣ ኢሉአባቦራ፣ ቡኖ በደሌ፣ ሁሉም የአርሲ፣ የባሌና የጉጂ ዞኖች፣ ምስራቅ ሐረርጌና የቦረና ዞን እንዲሁም ምዕራብና ምሥራቅ ጎጃም፣ መካከለኛው፣ የሰሜንና የምዕራብ ጎንደር፣ የባህር ዳር ዙሪያ፣ አዊ ዞን መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡
በተመሳሳይ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዞኖች፣ የሲዳማ ክልል ዞኖች፣ የሃዲያና ሃላባ ዞኖች፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፣ የሶማሌ ክልል ዞኖች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖራቸው ተመላክቷል፡፡
በተጨማሪም የጋምቤላ ክልል ዞኖች፣ የደቡብ ጎንደር፣ የሰሜንና የደቡብ ወሎ ዞኖች፣ የዋግ ኽምራ፣ የደቡብና የመካከለኛው ትግራይ ዞኖች፣ ምዕራብ ሐረርጌ፣ አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋና ሐረሪ በአንዳንድ ሥፍራዎቻቸው በአብዛኛው ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ይጠበቃል።