በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት ዓለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል ተባለ
አዲስ አበባ፣ መሰከረም 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት ዓለም አቀፋዊ ተቋማት የፋይናንስ ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ያለመ አህጉር አቀፍ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የተሳተፉት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴዔታ ሳንዶካን ደበበ÷አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እንደ ጎርፍ፣ ድርቅና ረሃብ የመሳሰሉ ችግሮችን እየተጋፈጠች መሆኑን አንስተዋል፡፡
በአፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቀልበስ ፖሊሲ ተቀርጾ እየተሰራ ቢሆንም ለማስፈፀሚያ የሚሆን የፋይናንስ አቅም ባለመኖሩ ጉዳዩ አሳሳቢ ሆኖ መቀጠሉን አብራርተዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት አንዳንድ ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ብቻ የሚያደርጉት ድጋፍ በቂ አለመሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአከባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን የገለፁት ሚኒስትር ዴዔታው÷ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ባለፉት አራት ዓመታት በርካታ ችግኝ መትከል መቻሉን ገልፀዋል፡፡
በመድረኩ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ድጋፍ በአከባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች ዙሪያ ያላቸው ተሞክሮ መቅረቡን ከፕላንና ልማት ሚኒስትር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡