በመዲናዋ በ10 ሺህ ተቋማት ላይ ብክለትን በሚመለከት ጥብቅ ቁጥጥር ሊደረግ ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ 10 ሺህ አምራችና አገልግሎት ሰጪ የመንግስትና የግል ተቋማት ላይ ብክለትን በሚመለከት ጥብቅ ቁጥጥር ሊደረግ ነው።
ቁጥጥር የሚደረገው የግልና የመንግስት ሆስፒታሎች፣ ሆቴሎች፣ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ሌሎችም አምራችና አገልግሎት ሰጪ የመንግስትና የግል ተቋማት ላይ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዳዲ ድሪባ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳስታወቁት፤ የአፍሪካ መዲና የሆችውን ከተማ ከብክለት መከላከል ይገባል።
በላብራቶሪ መሳሪያዎች በመታገዝ ከተቋማት የሚወጡ ብካዮችን በተመለከተ በየደረጃው ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደረግ ገልጸው፤ ባለስልጣኑ በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት እርምጃ እንደሚወሰድ አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም የድምፅ ብክለት ሊያደርሱ በሚችሉ የተለያዩ ተቋማት ላይ በልኬት መሳሪያ በመጠቀም ቁጥጥር ለማድረግ መዘጋጀታቸውንም ነው የገለጹት።
ባሳለፍነው 2015 ዓ.ም በጥቆማና በባለስልጣኑ ክትትል በ637 የተለያዩ የመንግስትና የግል ተቋማት ላይ ከማስጠንቀቂያ እስከ ገንዘብ ቅጣት ድረስ እርምጃ መወሰዱን አስታውሰዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ግን በተጠናከረ ሰው ኃይል ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ተቋማትን ማሸግን ጨምሮ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል።
በታሪክ አዱኛ