የልጃችን ከፍተኛ ውጤት የትጋቷ ፍሬ ነው – የተማሪ ሃናን ወላጆች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ልጃቸው ትምህርቷን በሚገባ ተከታትላ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገቧ ኩራትና ደስታ እንደተሰማቸው የ12ኛ ክፍል ከፍተኛ ውጤት ያመጣችው ተማሪ ሃናን ናጂ አህመድ ወላጆች ገለጹ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው የክሩዝ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዋ ሃናን የ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት 649 በማስመዝገብ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት አምጥታለች፡፡
ተማሪ ሃናን የ12ኛ ክፍል ፈተናን ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ እቅድ አውጥታ በሚገባ ስታጠና እንደነበር ትናገራለች፡፡
ብዙ ጊዜዋን በማንበብ እንደምታሳልፍ፣ አስተማሪ ከማስተማሩ በፊት ቀድማ የክፍለ ጊዜውን ትምህርት ይዘት እንደምታነብ፣ ይህ ልምድም አስተማሪው ሲያስተምር ጉዳዩን በደንብ እንድረትረዳ እንደሚያስችላት ትገልጻለች፡፡
ለሁሉም የትምህርት አይነቶች እኩል ትኩረት በመስጠት ለፈተናው አስፈላጊውን ዝግጅት ቀድማ ማጠቀቋን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸለች፡፡
ለሁሉም ነገር ትኩረት ሰጥተው ከሰሩ የማይሳካ ነገር የለም የምትለው ሃናን÷ ተማሪዎች ከሰው ከመጠበቅ ይልቅ ራሳቸውን ዝግጁ አድርገው ለውጤት መስራት አለባቸው ብላለች፡፡
ኢንተርኔትን ለትምህርቷ ግብዓት ለሚሆኑ መረጃዎች እንደምትጠቀም ገልጻ÷ አላማና ግብ አስቀምጣ አጥንታ ባገኘችው ውጤት ደስተኛ መሆኗንም አንስታ፤ በቀጣይ ፋርማኮሎጂ የማጥናት ፍላጎት እንዳላት ነው የነገረችን፡፡
የተማሪ ሃናን ናጂ እናት ወ/ሮ ሽኩሪያ ሽፋ እና አባት አቶ ናጂ አሕመድ በበኩላቸው÷ ልጃቸው በርትታ በማጥናት የልፋቷን ውጤት በማግኘቷ ከፍተኛ ኩራትና ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።
ተማሪ ሃናን ለትምህርቷ ልዩ ትኩረት እንደምትሰጥና ለየትኛውም የሚያዘናጋ ሁኔታ ቦታ እንደማትሰጥም አስረድተዋል፡፡
አላማዋን ለማሳካት እቅድ አውጥታ እያንዳንዱን ነገር ከመፈጸም ወደ ኋላ እንደማትል የሚናገሩት ወላጆች÷ በቀጣይ ጥሩ ደረጃ ላይ እንደምትደርስ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ተማሪዎች በትክክለኛው የህይወት መስመር እንዲጓዙ የወላጆች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው÷ ለዚህም አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
የልጃችን ከፍተኛ ውጤት የትጋቷ ፍሬ ነው በማለት ገልጸው፤ በዚሁ ቀጥላ ወደ ፊት የምትፈልግበት ደረጃ ላይ እንደምትደርስ በእርግጠኝነት ተናግረዋል።
በመላኩ ገድፍ