Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ አጠቃላይ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ድርሻ ወደ 30 በመቶ ለማሳደግ እየተሠራ ነው – አቶ ሽመልስ

 

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በሚቀጥሉት 15 ዓመታት ውስጥ የአጠቃላይ ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ድርሻ ከ19 ነጥብ 6 በመቶ ወደ 30 በመቶ ለማሳደግ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለፁ፡፡

ርእስ መስተዳድሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው÷ በተመሳሳይ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ሴክተሩን ከ12 ነጥብ 6 በመቶ ወደ 19 በመቶ ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ እነዚህ ግቦች እንዲሳኩ የትኩረት አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል ብለዋል።

ትኩረት ከምንሰጣቸው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች አንዱ አግሮ-ኢንዱስትሪ ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ፤ የዚህ ዓይነቱ ኢንዱስትሪ የግብርና ምርቶችን የሚያመርትና በግብአትነት የሚጠቀም እና ለግብርና ኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ቁሳቁሶችን የሚያመርት ነው ብለዋል።

በዚህ እንቅስቃሴ በገጠር ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ የተበታተነና የተጓተተውን የግብርና ኢኮኖሚ ወደ የተደራጀና የተፋጠነ የግብርና ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ምዕራፍ በማሸጋገር ገጠሩን በግብርና ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዞኖች አደራጅተን የምናለማ ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል።

በዚህም የተበታተኑ የገጠር መንደሮችን የግብርና ግብአት በሚፈልጉ የግብርና ኢንዱስትሪዎች ስር የምናደራጅ ይሆናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ከከተማ ጋር በመጣጣምና በመደጋገፍ እንዲራመዱ የምናቀናጅ ይሆናል ብለዋል።

“በማክሮ ኢኮኖሚ ደረጃም የኢንዱስትሪ እድገታችን የተሰናሰለ እና የሚደጋገፍ ሆኖ እንዲጓዝ የረዥም ጊዜ ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው” ሲሉም ገልፀዋል አቶ ሽመልስ።

ከሁሉ በላይ የግብርና ኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ የህብረተሰቡ የዕድገት ማዕከል፣ የሥራ ዕድልና የሀብት ባለቤት ለማድረግ ቅድሚያ ሰጥቶ እየተተገበረ ይገኛል ብለዋል።

ርእሰ መስተዳድሩ በየደረጃው ያለው አመራርና ባለድርሻ አካላት በዘርፉ የተቀመጡትን ዓላማዎች፣ ዕቅዶችና ግቦች ተረድቶ የድርሻውን እንዲያበረክት አሳስበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.