አቶ ቀጀላ መርዳሳ ከአሜሪካ ኤምባሲ ምክትል ሃላፊ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጀላ መርዳሳ ከአሜሪካ ኤምባሲ ምክትል ሃላፊ ጎንዲልን ዌንዲ ግሪን ጋር በቅርጫት ኳስ ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይቱ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የቅርጫት ኳስ ስፖርት ከተጀመረ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት የዘርፉ እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ መምጣቱን አንስተዋል፡፡
በዚህ ሰዓት በቅርጫት ኳስ ዙሪያ በትብብር መስራት ወሳኝ ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷ በተለይም አሜሪካ በቅርጫት ኳስ የምትታወቅ ሀገር በመሆኗ ኢትዮጵያ በዘርፉ ልምድና ድጋፍ ልታገኝ እንደምትችል አመላክተዋል፡፡
በቀጣይም በቅርጫት ኳስ ዙሪያ የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም ከኢትዮጵያ ባስኬት ቦል ፌዴሬሽን ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
የአሜሪካ ኤምባሲ ምክትል ሃላፊ ጋር ጎንዲልን ዌንዲ ግሪን በበኩላቸው÷ በቅርጫት ኳስ ስፖርት ዙሪያ ወጣቶችን በማሳተፍ መስራት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በስፖርቱ የሴቶችን ተሳትፎ ከወንዶች እኩል ለማድረግና ለማሳደግ እንሰራለን ማለታቸውን ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡