በዚህ ዓመት 200 ሺህ የሚደርሱ የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ማህበረሰቡ ለመቀላቀል ታቅዷል ተባለ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 30 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በዚህ ዓመት 200 ሺህ የሚደርሱ የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ማህበረሰቡ ለመቀላቀል መታቀዱን የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ተሾመ ቶጋ ገለጹ።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ተሾመ ቶጋ ከጥር 2015 ዓ.ም ጀምሮ ኮሚሽኑ የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ በማስፈታት ወደ ማህበረሰቡ ለመቀላቀል የሚያግዙ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ጠቅሰዋል።
በሀገሪቱ ስምንት ክልሎች በውጊያ ላይ ሲሳተፉ የነበሩ 371 ሺህ 971 የቀድሞ ተዋጊዎችን መለየቱን ያነሱት ኮሚሽነሩ፥ በዚህ ዓመትም ከ150 ሺህ እስከ 200 ሺህ ያህሉ አስፈላጊውን የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ይደረጋል ብለዋል።
በጦርነት አውድ ውስጥ የቆየውን የተዋጊዎችን ስነ ልቦና ለሰላምና ምርታማነት ለማዘጋጀት አዕምሯዊ ዝግጅት፣ የፖለቲካ ግንዛቤና ማህበራዊ ተሃድሶ ለመስጠት የሚያስችሉ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ኮሚሽኑ ስራውን ለማከናወን የሚያግዘውን የሁለት ዓመት ፕሮግራምና ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ አስፈላጊውን ገንዘብ ለማግኘት ከዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ የልማት አጋሮች ጋር ውይይት ማድረጉንም ተናግረዋል።
የቀድሞ ተዋጊዎች ስልጠና የሚያገኙባቸው ማዕከላት ግንባታና የማሰልጠኛ ሰነዶች አለመጠናቀቃቸውን ገልፀው በቀጣይ እነዚህን ለማሳካት ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ለአብነትም እያንዳንዳቸው 5 ሺህ የቀድሞ ተዋጊዎችን መያዝ የሚችሉ 5 ትላልቅ ማዕከላትን በ500 ሚሊየን ብር መልሶ ለመገንባት ከመከላከያ ሚኒስቴርና ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር እየተሰራ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።
በተሃድሶ ፕሮግራሙ በተለያዩ ምዕራፎች ተዋጊዎቹን ወደ ማህበረሰቡ ለመቀላቀል መታቀዱን ጠቅሰው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሸኛቸው 50 ሺህ የቀድሞ ተዋጊዎችም በፕሮግራሙ እንደሚሳተፉም ነው የተናገሩት።
መንግስት ለተሃድሶ መርሐ ግብሩ መሳካት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን በመጥቀስም፥ የሀገር ውስጥ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች፣ ባለሀብቶችና ሌሎችም በልዩ ልዩ መንገድ የኮሚሽኑን ተልዕኮ ለመሳካት እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል።