Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የአለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ያወጣውን ሪፖርት እንደማትቀበለው ገለፀች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)ኢትዮጵያ የአለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ሁኔታ ላይ ያወጣውን ሪፖርት እንደማትቀበለው አስታወቀች፡፡

የአለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና የዘር ፍጅት ስጋት አለ በሚል ያወጣውን መግለጫ በመቃወም የኢፌዲደሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ አውጥቷል፡፡

ሚኒስቴሩ በመግለጫውም÷ ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ በተከሰቱ ግጭቶች ያለውን ወቅታዊ የሰብዓዊ ሁኔታ በተመለከተ ባወጣው ሃላፊነት የጎደለው እና መሰረተ ቢስ ክስ የኢትዮጵያን መንግስት አሳዝኖታል ብሏል፡፡

የኮሚሽኑ ሪፖርት ትክክለኛ የምርመራ ሂደትን ያልተከተለ እና ከትክክለኛ ምንጮች ያልተወሰደ እንዲሁም በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ መሬት ላይ ያለውን እውነታ የማይገልፅ መሆኑን ጠቅሷል።

በሰሜኑ ክፍል የተከሰጠውን ጦርነት ለማስቆም ባለፈው ዓመት በደቡብ አፍሪካ የፕሪቶሪያ ስምምነት መፈረሙን ያስታወሰው ሚኒስቴሩ÷ በዚህም በሰሜን የሀገራችን ክፍል የጥይት ድምፅ እንዳይሰማ ማድረግ መቻሉን አንስቷል፡፡

መንግስት የፕሪቶሪያው ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ቁርጠኛ መሆኑን እንዲሁም ግልፅነትና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችል ተግባር እያከናወነ እንደሆነ ጠቅሷል።

በዚህም በኢትዮጵያ ቀደም ሲል የነበሩ እና አሁንም ያሉ ቅሬታዎችን ለመፍታት ወደ ሰላም ለመምጣት በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኩል እየተሰራ እንደሆነም አንስቷል።

እንዲሁም የሽግግር ፍትህ ለማስፈን የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

ይህ ባለበት ሁኔታ በተመድ የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከሽፏል በሚል የቀረበው ሃሳብ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስገንዝቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.