ፍ/ቤቶች ፍትሃዊ፣ ነጻና ገለልተኛ ሆነው አገልግሎት እንዲሰጡ ዝግጅት ተደርጓል – አቶ ቴዎድሮስ ምህረት
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)የፌዴራል ፍ/ቤቶች ፍትሃዊ፣ ነጻና ገለልተኛ ሆነው ለሕብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ዝግጅት መደረጉን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት ገለጹ፡፡
የፌደራል ፍርድ ቤቶች መደበኛ የዳኝነት አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተካሂዷል።
በዚህ ወቅት እንደተገለጸው÷ የፌደራል ፍርድ ቤቶች ከነሐሴ 1 ቀን 2015 ዓ.ም እስከ መስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም ቀን ድረስ በከፊል ዝግ ሆነው ቆይተዋል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት÷ ፍርድ ቤቶች የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የማይተካ ሚና አላቸው ብለዋል።
በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት የፌዴራል ፍ/ቤቶች እንደቀደመው ጊዜ ሁሉ ፍትሐዊ፣ ነጻና ገለልተኛ ሆነው ለህብረተሰቡ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ፍርድ ቤቶች የአገልግሎት አሰጣጣቸውን በማዘመንና ራሳቸውን በማሻሻል በሕዝብ ዘንድ ያላቸው አመኔታ እንዲጨምር በማድረግ ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ቀልጣፋ፣ ጥራት ያለውና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚሰራም መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በፍርድ ቤቶች እየተተገበሩ የሚገኙ የለውጥ ስራዎችም የዳኝነት ገለልተኝነት መርህን በጠበቀ መልኩ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
በዛሬው ዕለት በይፋ አገልግሎት የጀመሩ ፍርድ ቤቶችም የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ናቸው።