በሩብ ዓመቱ ስኬታማ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ሥራ መከናወኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ወዳጅ በማብዛትና ጠላት በመቀነስ ስኬታማ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ማከናወን መቻሏን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም÷ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የተከናወኑ ዲፕሎማሲያዊ ሁነቶችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
ቃል አቀባዩ እንዳሉት፣ በበጀት ዓመቱ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ወደ መደበኛ በመመለስ አጋር ማብዛት የሚል በመሆኑ ብሔራዊ ጥቅማችንን ማረጋገጥ የሚያስችል ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራ ማከናወኗን ገልጸዋል።
ዋና ግቡም ጠላትን በመቀነስ ወዳጅ ማብዛት መሆኑን የገለጹት አምባሳደር መለስ÷ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ከአውሮፓ ህብረት፣ ከአሜሪካ፣ ከቻይናና መሰል ዓለም ዓቀፍ ተቋማትና ሀገራት ጋር የነበረው የዲፕሎማሲ መስተጋብር ዘርፈ ብዙ ውጤቶች የተመዘገቡት ነበር ብለዋል።
ለአብነትም ከአሜሪካ መንግስት ጋር በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ የልማት ትብብር፣ ዲሞክራሲ፣ ሰብዓዊ መብትና መልካም አስተዳደር እንዲሁም በመከላከያና ጸጥታ ጉዳይ ምክክር እየተደረገ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከ78ኛው የተመድ ስብሰባ ጎን ለጎን ከ30 በላይ የሀገር መሪዎች፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ተቋማት ሀላፊዎች ጋር መነጋገራቸውን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ ያደረገው የፋይናንስ ድጋፍም በሩብ ዓመቱ የተመዘገበው የዲፕሎማሲ ስኬት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ክሮሽያ፣ ኮሎምቢያ እና መሰል ሀገሮች በኢትዮጵያ ኤምባሲያቸውን ለመክፈት ፍላጎታቸውን እያሳዩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።