Fana: At a Speed of Life!

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ከጋምቤላ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር በትምህርት ጥራት ዙሪያ እየተወያዩ ነው፡፡

ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በዚሁ ጊዜ እንዳሉት÷ የትምህርት ጥራትን የማረጋገጡ ስራ ለመንግስት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ሀገር ተረካቢ እና በሥነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ ለማፍራት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ ነው።

ሚኒስትሩ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አንስተዋል፡፡

እንደ ሀገር ከተመዘገበው ዝቅተኛ ውጤት በመነሳት ከሁሉም ባለድርሻዎች ጋር በመቀራረብና በመመካከር የትምህርት ጥራትንና የተማሪዎችን ውጤት በዘላቂነት ለማሻሻል እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

በተለይም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በጋምቤላ ክልል የተመዘገበው ውጤት እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ÷ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው በመስራት የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው÷ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ምቹ የትምህርት አካባቢን መፍጠር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት የትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚጠበቅ ከጋምቤላ ክልል ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ሚኒስትሩ በነገው ዕለት በጋምቤላ በሚኖራቸው ቆይታ ከተለያዩ የትምህርት ዘርፍ ባለድርሻ አካላትና ከጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ሰራተኞች ጋር ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.