አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከጣሊያን፣ ጀርመን እና ፈረንሳይ አምባሳደሮች ጋር መከሩ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከጣሊያን፣ ጀርመን እና ፈረንሳይ አምባሳደሮች ጋር ተወያዩ፡፡
አምባሳደር ምስጋኑ ፥ ከጣሊያን አምባሳደር አጎስቲኖ ፓሌሴ፣ ከጀርመን አምባሳደር ስቴፋን አውየር እና ከፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ተወያይተዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ በኢትዮጵያ እና በሀገራቱ መካከል በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን መድረኮች ላይ ያለውን ትብብር የሚደነቅ እንደሆነ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሂደት፣ የሽግግር የፍትህ አሰራር እና የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን ለመፍታት ያለመ እና የብሄራዊ የውይይት ሂደት ያለውን ጠቀሜታም ነው ያመለከቱት።
የጣሊያን አምባሳደር አጎስቲኖ ፓሌዝ ኢትዮጵያ በቀጠናው ያላትን ቁልፍ ሚና ጠቁመው ፥ የጣሊያን መንግስት በጋራ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነት ጠቅሰዋል ።
የጀርመን አምባሳደር ስቴፋን አውየር በበኩላቸው ፥ መንግስታቸው ከኢትዮጵያ ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ቁርጠኝነት እንዳለውም ነው ያረጋገጡት።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ እና ቀጣናዊ ትብብር ላይ እያበረከተች ያለችውን ሚናም ማድነቃቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የፈረንሳዩ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ ፥ የፈረንሳይ መንግስት ለፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ትግበራ እና ለተጀመረው የእርቅ እና የመልሶ ማቋቋም ስራዎች ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው ያረጋገጡት።
ሚኒስትር ዴኤታው የአውሮፓ ህብረት በመልሶ ማቋቋም እና ትጥቅ ማስፈታት፣ ማሰባሰብ እና መልሶ ማቋቋም ፕሮግራም ላይ ተግባራዊ እና ተጨባጭ ስራ እንዲሰራም ጠይቀዋል።