የተሻለ ትምህርት መስጠት ካልተቻለ እንደማኅበረሰብ እንከሥራለን- ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለልጆቻችን የተሻለ ትምህርት መስጠት ካልተቻለ እንደማኅበረሰብ ትልቁን ኪሳራ ነው የምናስተናግደው ሲሉ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ተናገሩ፡፡
ሚኒስትሩ በጋምቤላ ከተማ የሚገኙትን የኢሌይ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጎብኝተዋል፡፡
ከጉብኝታቸው በኋላ ከትምህርት አስተዳደር አካላት፣ ከመምህራን እና ከተማሪዎች ጋር በትምህርት ሂደቱ ዙሪያ መክረዋል፡፡
በውይይታቸውም ትምህርት ቤቶቹ ላለፉት በርካታ ዓመታት ዜጎች ተምረው የወጡባቸው ቢሆንም በተፈለገው የትምህርት ጥራት ደረጃ አልሠሩም ብለዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታትም የ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና ከወሰዱ በርካታ ተማሪዎች ያለፉት ተማሪዎች ቁጥር እጅግ በጣም ጥቂት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ለዚህም ተጠያቂዎቹ መንግሥት፣ የትምህርት አስተዳደር ሠራተኞች እና መምህራን ናቸው ማለታቸውን ከጋምቤላ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ባለፉት በርካታ ዓመታት በክልሉ የፈተና ኩረጃና ስርቆት ተስፋፍቶ እንደነበር አስታውሰው÷ በአቋራጭና በኩረጃ የሚገኝ ውጤት ከዚህ በኋላ አይኖርም ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡
በአንድ ጀንበር ለውጥ ማምጣት ባይቻልም ለቀጣዩ ትውልድ ውጤት መሻሻል ሲባል ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።