የተሃድሶ ኮሚሽን እና ም/ቤቱ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ፈረሙ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ፈረሙ፡፡
ስምምነቱን የፈረሙት÷ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ም/ቤት ተወካይ ዋና ዳይሬክተር ሃና ወልደ ገብርኤል ናቸው፡፡
በስምምነቱ መሰረት የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ በማቋቋም ወደ ሲቪል ሕይወት ለመመለስ በሚከናወኑ ሥራዎች ላይ ተቋማቱ በጋራ ይሠራሉ፡፡
በዚህም ሃብት ማሰባሰብ፣ የግንዛቤ የማስጨበጫ ሥራዎችን በማከናወን፣ መረጃ በመለዋወጥ እና በአቅም ግንባታ ሥራዎች ዙሪያ በጋራ ለመሥራት ተስማምተዋል፡፡
የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ቀደመ ሕይወታቸው የመመለስ ሥራው የሁሉንም አካላት ትብብር እንደሚፈልግ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
ዛሬ የተደረገው ስምምነትም ትልቅ ጅማሮ መሆኑን ጠቁመው በተለያዩ አካባቢዎች ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ስምምነቱ ተግባራዊ ሆኖ የሚጠበቀውን ውጤት እንዲያመጣም በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ሃና ወልደ ገብርኤል በበኩላቸው÷ የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ቀድሞ ሕይወታቸው የመመለስ ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆን ምክር ቤቱ የሚጠበቅበትን ሚና እንደሚወጣ አረጋግጠዋል፡፡