ኮሚሽኑ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአጀንዳ ልየታ የሚሳተፉ ተወካዮችን ማስመረጥ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስተባባሪነት በአጀንዳ ልየታ የሚሳተፉ ተወካዮችን የማስመረጥ ስራ ተጀምሯል።
የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ብሌን ገ/መድን÷ በአጀንዳ ልየታ የሚሳተፉ ተሳታፊዎችን የማስመረጥ ስራ በየዞኑ የሚካሄድ ሲሆን የመጀመሪያው ዙር ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ይካሄዳል ብለዋል፡፡
በአሶሳ ዞን እና በከተማ አስተዳደሩ ስር የሚገኙ የ10 ወረዳዎች በድምሩ 1 ሺህ 170 ተሳታፊዎች ወኪሎቻቸውን የሚመርጡበት የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁን ገልፀዋል።
የሚካሄደው የተወካዮች ምርጫ ሁሉን የማህበረሰብ ክፍል ያካተተ፣ ተአማኒ፣ ቅቡልነት ያለው እና የተሳካ እንዲሆን በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።