የሰንደቅ ዓላማ ቀን የፊታችን ሰኞ ይከበራል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰንደቅ ዓላማ ቀን የፊታችን ሰኞ ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚከበር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቋል፡፡
ቀኑ “የሰንደቅ ዓላማችን ከፍታ ለሕብረ-ብሔራዊ አንድነታችንና ለሉዓላዊነታችን ዋስትና ነው” በሚል መሪ ሃሳብ ለ16ኛ ጊዜ ነው የሚከበረው፡፡
ሀገራዊ ወቅታዊ ሁኔታን በዋጀ መልኩ ከሰንደቅ ዓላማ መርሆች ጋር ተገናዝቦና ሀገራዊ ሪፎርሙን በሚያስቀጥሉ ውይይቶች ታጅቦ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሪነት በመላ ሀገሪቷ እንደሚከበር ተጠቁሟል፡፡
የበዓሉ መከበር ለሕብረ-ብሔራዊ አንድነት እና ለሉዓላዊነት መጠናከር መነቃቃትን ለመፍጠር ትልቅ ትርጉም እንደሚኖረው ተጠቅሷል፡፡
ለሀገር ክብር እና ጥቅም ሁላችንም የበኩላችንን ለመወጣት በሰንደቅ ዓላማ ፊት ዳግም ቃላችንን የምናድስበት ዕለት ይሆናል ነው ያለው ምክር ቤቱ፡፡
በዓሉ በፌዴራል የመንግስት ተቋማት፣ በክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች፣ በመከላከያ ሠራዊት ካምፖች እንዲሁም በኤምባሲዎች እና የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች በተመሳሳይ ሰዓት ከረፋዱ 4 ሰዓት ተኩል ላይ በደማቅ ሁኔታ እንደሚከበር ተገልጿል፡፡