በ390 ሚሊየን ብር የተገነባው የኦክስጅን ማምረቻ ፋብሪካ የሙከራ ምርት ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በ390 ሚሊየን ብር ወጪ ያስገነባው ዘመናዊ የኦክስጅን ማምረቻ ፋብሪካ የሙከራ ምርት መጀመሩን አስታውቋል፡፡
የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አሸናፊ ታዘበው እንደተናገሩት÷ የኦክስጅን ማምረቻ ፋብሪካው መቋቋም ሆስፒታሉ ለኦክስጅን ግዢ በዓመት የሚያወጣውን 7 ሚሊየን ብር ወጪ ማዳን የሚያስችል ነው፡፡
ሆስፒታሉ የኦክስጅን ፍላጎቱን ለማሟላት ከዚህ በፊት ከአዲስ አበባ እና ባህር ዳር ሲያስመጣ መቆየቱን አንስተው÷ በግዢና በማጓጓዝ ሂደት በሚፈጠር መጓተት የህሙማን ህይወት አደጋ ላይ ሲወድቅ እንደነበረም ጠቅሰዋል።
የሆስፒታሉ የኦክስጅን ፍላጎት እያደገ መምጣቱን የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚው÷ በአሁኑ ወቅት በቀን እስከ 120 ሲሊንደር ኦክስጅን ጥቅም ላይ እንደሚያውል አስረድተዋል፡፡
በሆስፒታሉ የጽኑ ህሙማን የድንገተኛ አደጋዎችና የቀዶ ህክምና ክፍሎች ከፍተኛ የኦክስጅን ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁመው ÷ ይህን ለማሟላት ፋብሪካው መቋቋሙ ለህሙማን የተሟላና አስተማማኝ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ብለዋል፡፡
የኦክስጅን ማምረቻው በተገባደደው ሳምንት የሙከራ ምርት ማምረት መጀመሩንና በተያዘው ወር ወደ ሙሉ ማምረት ይሸጋገራል ተብሎ እንደሚጠበቅ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የኦክስጅን ምርቱን ጎንደር ከተማን ጨምሮ በሰሜን፣ በማዕከላዊና በምዕራብ ጎንደር ዞኖች ለሚገኙ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች በተመጣጣኝ ዋጋ በቅርቡ ማቅረብ እንደሚጀመርም ገልጸዋል፡፡
የኦክስጅን ማምረቻ ፋብሪከው በቀን ከአንድ ሺህ በላይ ሲሊንደሮችን የተጣራ ኦክስጅን የመሙላት አቅም እንዳለውም ተመላክቷል፡፡