እኩይ አላማቸውን ባልተገባ መንገድ ለመፈጸም የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ የተመራ ልዑካን ቡድን በባህር ዳር ከተማ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ጎብኝቷል።
ልዑካኑ በጉብኝታቸው÷ በከተማዋ በመንግስት የተሰሩ የሕዝብ መናፈሻ ቦታዎችንና የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡
አቶ አደም ፋራህ ÷ የባህር ዳር ከተማን የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን በጉብኝቱ ወቅት ተናግረዋል።
በክልሉ አብዛኛው አካባቢ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን የገለጹት ምክትል ፕሬዚዳንቱ÷ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ሕዝብን በማስተባበር በፍጥነት ወደ ልማት መመለስ ይገባቸዋል ብለዋል።
በክልሉ የሚገኘው ጽንፈኛ ሃይል የክልሉን ሕዝብ ሰላም ለመንሳትና በሕዝብ የተመረጠን መንግስት በሃይል ለመንጠቅ እንቅስቃሴ ሲያደርግ መቆየቱን አንስተዋል፡፡
መንግስት የሕግ የበላይነት የማስከበር ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውንም የብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው÷ በፈተናዎች ውስጥ ሆነን ልማት ማምጣት እንደሚቻል በባህር ዳር የተሰሩ የሕዝብ መናፈሻዎች ምስክሮች ናቸው ብለዋል።
እርስ በእርስ በመጠፋፋት የህዝብ ጥያቄዎችን መመለስ አይቻልም ያሉት አቶ ተስፋዬ÷ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ክልሉ ወደ ቀድሞ ሰላሙ ሙሉ በሙሉ እንዲመለስ መስራት እንዳለባቸው አመላክተዋል።
ዘላቂ ሰላም ለማምጣት መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው÷ ጥያቄ አለኝ የሚል ማንኛውም አካል በጠረንጴዛ ዙሪያ ለመወያየት መንግስት በሩ ክፍት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በከተማዋ ሰፋፊ የመሰረተ ልማት ስራዎች ተጀምረው በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው ናቸው፡፡
በከተማዋ የአረንጓዴ ልማት ስራዎች በትኩረት እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸው÷የልማት መሰረቱ ሰላም ነው ፤ሰላም ከሌለ የሕዝብን ጥያቄዎች በአግባቡ መመለስ እንደማይቻል አጽንኦት ሰጥተዋል።