ከዚህ ቀደም ለልማት ስራ ባልዋለ አካባቢ የቅባት እህል በስፋት እየለማ ነው – አቶ እንዳሻው ጣሰው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከዚህ ቀደም ለልማት ስራ ያልዋለና በረሀማ የሆነ አካባቢ ለዘይት ፋብሪካ በግብአትነት የሚውል የቅባት እህል በስፋት እየለማ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው ገለጹ።
የተፈጥሮ ጸጋን በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል በግል ባለሀብቶች እየለማ ያለው ሰብል ማሳያ እንደሆነም ተናግረዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው፣ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ባለሃብቶች በጉራጌ ዞን በበላይነህ ክንዴ ኢንቨስትመንት ግሩፕ እየለማ ያለ የቅባት ሰብል ጎብኝተዋል።
አቶ እንዳሻው በወቅቱ እንደገለጹት፥ በክልሉ ከዚህ ቀደም ለልማት ስራ ያልዋለና በርሀማ በሆነ አካባቢ የኢትዮጵያን ምርት ሊያሳድግና ለዘይት ፋብሪካ ግብዓት የሚሆን የቅባት እህል በስፋት እየለማ ነው።
የዘይት ምርትን ለማሳደግ የቅባት ሰብሎችን ማልማት ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
በክልሉ እየተንቀሳቀሱ ያሉ አልሚ ባለሃብቶች ለህብረተሰቡ በስራ እድል ፈጠራ፣ በመሰረተ ልማት አቅርቦትና በሌሎችም መስኮች የህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።
በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኡስማን ሱሩር እንደገለጹት፥ ግብርናውን ለማዘመንና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለማስቀረት ዘርፈ ብዙ ስራ እየተከናወነ ነው።
ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆን የሱፍ፣ የሰሊጥ፣ የአኩሪ አተርና ሌሎች ሰብሎችን በስፋት የሚያመርቱ ባለሃብቶችን መፍጠር መቻሉን አስረድተዋል።
በክልሉ ያለውን ጸጋ ለአልሚ ባለሃብቶች ምቹ በማድረግና የግብርና ኢንቨስትመንት ወደላቀ ደረጃ በማሸጋገር ሀገራችን ለሌሎች ሀገሮች መርዳት የምትችልበትን እድል ለመፍጠር መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ባለሃብቱ በላይነህ ክንዴ በጉብኝት መርሐ ግብሩ ላይ፥ ከድህነት ጋር ታርቀን መኖር ይበቃናል ብለዋል።
መሬትን፣ ጉልበትንና ውሃን አቀናጅተን ከሰራን ያለንን የድህነት ታሪክ በአጭር ጊዜ መቀየር እንችላለን ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በጉራጌ ዞን እየተካሄደ ባለው ኢንቨስትመንት 400 ዜጎች የስራ እድል እንደተፈጠረላቸውም ነው ያነሱት።
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!