ኢትዮጵያ እና ደቡብ ኮሪያ በንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ አስታወቁ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ደቡብ ኮሪያ ያላቸውን የጠነከረ ግንኙነት በቢዝነስ እና በኢንቨስትመንት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ በኢትዮጵያ ከደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ካንግ ሲዩኪሄ ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ የተካሄደው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውንና ለረጅም ዓመታት የዘለቀውን ግንኙነት በቢዝነስና በኢንቨስትመንት ለማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ እንደሆነም ነው የገለጹት።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ ፥ በኢትዮጵያ እና ደቡብ ኮሪያ መካከል ያለው ነባር ግንኙነት በደምና በአጥንት ጭምር መሰረት ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ይህንን ይበልጥ ለማጠናከር በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ አፅንኦት ሰጥተዋል።
አክለውም ፥ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በተለይም በማምረቻው ዘርፍ አዳዲስ የደቡብ ኮሪያ ባለሀብቶች እንዲሰማሩ ለማስቻል ይበልጥ ተቀራርቦ መስራት እንደሚገባ ነው የጠቀሱት።
በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ካንግ ሲዩኪሄ በበኩላቸው ፥ በኢትዮጵያ እና ደቡብ ኮሪያ መካከል ያለው ግንኙነት ከታሪክ ባሻገር ወደ እድገት ፣ ልማትና ኢንቨስትመንት ትብብር ማደግ እንዳለበት አንስተዋል፡፡
በቀጣይም በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በመሳተፍ ከኢትዮጵያ ጋር በዘርፉ ዋነኛ አጋር ሆነው መቀጠል እንደሚሹም ነው ያስታወቁት።
በውይይቱ መሰረት በኢንቨስትመንትና ቢዝነስ ፣ በስልጠናና በትምህርት መስኮች እንዲሁም በሌሎች መሰል የአጋርነት ዘርፎች በቅንጅት ለመስራት ከስምምነት መደረሱን ከኮርፖሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!