Fana: At a Speed of Life!

በሙስና ወንጀል የተከሰሱ 4 የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ሰራተኞች ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ተሰጠ

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ያለ አግባብ የሲሚንቶ ግዢ በመፈፀም ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ ለግል ጥቅም አውለዋል ተብለው በሙስና ወንጀል የተከሰሱ 4 የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ሰራተኞች ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ተሰጠ።

በተከሰሱበት አንቀጽ የጥፋተኝነት ፍርድ የተሰጠባቸው ተከሳሾች 1ኛ የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ተቋም የኮንስትራክሽን እና ሎጂስቲክስ ም/ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ደሜ፣ በተቋሙ የግዢ ባለሙያ ናቸው የተባሉ ቱጅባ ቀልቤሳ እና ሙስጠፋ ሙሳ ናቸው።

የጥፋተኝነት ፍርዱን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው፡፡

ተከሳሾቹ የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ተቋም የግዢ ፍላጎት ሳይኖረው ትዕዛዝ ባልተሰጠበት እና ከተቋሙ ዕውቅና ውጪ የግዢ ባለሙያ ሆነው ሲሰሩ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ በ2013 እና 2014 ዓ.ም በተለያዩ ቀናቶች ለተቋሙ ነው በሚል ከሁለት ፋብሪካዎች የገዙትን 29 ሺህ 200 ኩንታል ሲሚንቶ ምርት በተለያዩ ቀናቶች ለግለሰቦች በመሸጥ ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል በማለት ዐቃቤ ህግ ታህሳስ 3 ቀን 2015 ዓ.ም በዋለው ችሎት በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ስልጣንን አላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መስርቶባቸው ነበር።

ተከሳሾቹ ክሱ ከደረሳቸውና በንባብ ከተሰማ በኋላ ወንጀሉን አልፈጸምንም ሲሉ የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ህግ ለወንጀሉ መፈጸም ያስረዱልኛል ያላቸውን ሶስት ምስክሮችን አቅርቦ አሰምቷል፤ በተያያዥ የሰነድ ማስረጃዎችንም አቅርቧል።

የዐቃቤ ህግን የምስክሮች ቃል ያዳመጠው ችሎቱ የምስክር ቃል መርምሮ ተከሳሾቹ በተከሰሱበት አንቀጽ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቶ ነበር።

ሆኖም ተከሳሾቹ በተለያዩ ቀናቶች ያቀረቡትን የመከላከያ ማስረጃ የመረመረው ፍርድ ቤቱ ዛሬ በዋለው የችሎት ቀጠሮ 1ኛ የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ተቋም የኮንስትራክሽን እና ሎጂስቲክስ ም/ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ደሜ ፣ በተቋሙ የግዢ ባለሙያ ናቸው የተባሉት ቱጅባ ቀልቤሳ እና ሙስጠፋ ሙሳን በተከሰሱበት አንቀጽ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል።

ተከሳሾቹ በተከሰሱበት ድንጋጌ ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት ነው ጥፋተኛ የተባሉት።

ከተሳሾቹ ጋር ቀደም ብሎ ክስ ቀርቦበት የነበረና ከዚህ በፊት በነበረ ቀጠሮ በችሎቱ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶት የነበረው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ተቋም የኮንስትራክሽን እና ሎጂስቲክስ ግዢ ፋይናንስ ክፍል ኃላፊ አቶ አሸናፊ ተስፋዬ በሚመለከት የዐቃቤ ህግ ማስረጃን በተገቢው ተከላክሏል በማለት በነጻ አሰናብቶታል።

ይሁንና ዐቃቤ ህግ ነጻ የተባለው ተከሳሽን በሚመለከት ይግባኝ እንደሚጠይቅ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት
አረጋግጧል፡፡

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.