Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ የዲፕሎማቲክና ሰርቪስ ፓስፖርት ለያዙ ዜጎች ቪዛን ለማስቀረት የሚያግዙ አዋጆችን አጸደቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያና በደቡብ ኮሪያ እንዲሁም በህንድ መካከል የዲፕሎማቲክና ሰርቪስ ፓስፖርት ለያዙ ዜጎች ቪዛን ለማስቀረት ያግዛሉ የተባሉ አዋጆችን መርምሮ አጽድቋል፡፡

6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ በዛሬው እለት ተካሂዷል፡፡

ምክር ቤቱ በስብሰባው÷ በኢትዮጵያ እና ደቡብ ኮሪያ እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በህንድ መንግስታት መካከል የዲፕሎማቲክና ሰርቪስ ፓስፖርት ለያዙ ሰዎች ቪዛ ለማስቀረት የተደረገውን ስምምነት ነው ያጸደቀው፡፡

ስምምነቱ የሀገራቱ ዜጎች ለስራ ጉዳይ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የተሳለጠና ምቹ እንዲሆን ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም ምክር ቤቱ በኢትዮጵያና በሊባኖስ መንግሥታት መካከል በሥራ ስምሪት ዘርፍ የተፈረመውን ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለዝርዝር እይታ ለሰው ሀብት ልማት ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡

በኢትዮጵያ እና በሩሲያ መካከል በሁለትዮሽ ወታደራዊ ቴክኒካዊ ትብብር ወቅት የተገኙ የአዕምሯዊ የፈጠራ ሥራ ውጤቶችና ንብረቶች የጋራ ጥበቃ ስምምነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለውጭ ግንኙነትና ለሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡

ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት የበለጠ ለማጠናከር የተፈረመ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን÷በሁለትዮሽ ወታደራዊ የቴክኒካል ትብብር ሂደቱ ውስጥ በአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ መስክ የተሻለ የጋራ መግባባትና ትብብር እንዲኖር ለማድረግ የሚያግዝ ነው ተብሏል፡፡

የአፍሪካ መድሐኒቶች ኤጀንሲ ማቋቋሚያ ስምምነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለዝርዝር እይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡

በኢትዮጵያ እና በፓኪስታን መንግስት መካከል የተደረገ የሁለትዮሽ ንግድ ስምምነትን ለማጽደቅ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡

የንግድ ስምምነቱ ኢትዮጵያ ከፓኪስታን ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት ለማሳደግ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር ባሻገር የኢትዮጵያን ንግድ ከቀሪው ዓለም ጋር ለማስተሳሰር እየተደረገ ያለውን ጥረት ከማገዝ አንጻር የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም የምክር ቤቱ 3ኛ አመት የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለ ጉባዔንም ምክር ቤቱ በስብሰባው መርምሮ አጽድቋል፡፡

በየሻምበል ምሕረት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.