በቁጭት የተጀመረው የግብርና ሥራ ስኬታማ ነው – አቶ እንዳሻው ጣሰው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እንደ ሀገር በግብርና ላይ በቁጭት የተጀመረው ሥራ በተግባር ለውጥ እያሳየ ነው ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው ገለጹ፡፡
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በወቅታዊ የተቀናጀ የግብርና ልማት ሥራዎች ላይ ያተኮረ የንቅናቄ መድረክ በቡታጅራ ከተማ እየተካሔደ ነው፡፡
አቶ እንዳሻው በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ክልሉ ቡናን ጨምሮ የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን እንዲሁም የሰብል ምርቶችን ለማምረት ምቹ ነው ብለዋል፡፡
ይህም ለሥራችን ትልቅ እገዛ ያደርጋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ አሁን የሚያስፈልገው በኅብረት መሥራት ነው ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ሰብል ላይ ወይም ፍራፍሬ ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ ሁሉንም ማምረት ውጤታማ ስለሆነ ሥራው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባልም ነው ያሉት።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኡስማን ሱሩር በበኩላቸው÷ በክልሉ ውኃን ማዕከል ያደረገ የግብርና ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
ክልሉ ለሁሉም ዓይነት ምርት ቢመችም ካለው ሀብትና ተፈጥሮ አንፃር ገና ብዙ ሥራ እንደሚቀር ጠቁመው÷ ለአርሶአደሩ የግብዓት አቅርቦትን ከማመቻቸት ባለፈ በመንግሥት በኩል ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
በክልሉ በበጋ መስኖ እየለማ ከሚገኘው 147 ሺህ 683 ሔክታር ከ33 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እእንደሚጠበቅ ጠቅሰዋል፡፡
የግብርና ምርታማነትን ማሳደግና ማዘመን የንቅናቄው ትኩረት መሆኑን የገለጹት አቶ ኡስማን÷ ንቅናቄው በዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ጭምር እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡
በታሪክ አዱኛ እና ጥላሁን ይልማ