በኦሮሚያ ክልል የተከሰተውን ወረርሽኝ የመከላከል ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ቦታዎች የተከሰተውን የኮሌራ እና የወባ ወረርሽኝ እንዲሁም በተወሰኑ ቦታዎች ሰብል ላይ የተከሰተውን የግሪሳ ወፍ ወረርሽኝ የመከላከል ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ።
የክልል የቡሳ ጎኖፋ የቅድመ ማስጠንቀቂያና የአደጋ ስጋት ቅነሳ ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ ቤኛ ዱሬሳ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳስታወቁት፤ የወባ ወረርሽኝ በተከሰተባቸው ቄለም ወለጋና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች የመከላከል ስራ እየተሰራ ነው።
የኮሌራ ወረርሽኝን በተመለከተም በጉጂና ቦረና ዞኖች እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ከሚመለከታቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ አጋሮች ጋር በመቀናጀት የመከላከል ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የግሪሳ ወፍ ወረርሽኝ የተከሰተባቸው አርሲ፣ ምስራቅ ሐረርጌና ምስራቅ ሸዋ አካባቢዎች በሰብል ላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ከግብርና ባለሙያዎች ጋር በቅንጅት የመከላከል ስራ እየተሰራ መሆኑን ኃላፊው ጨምረው ገልጸዋል።
በክልሉ የሚከሰቱ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች በተቀናጀ መንገድ ምላሽ በመስጠት ረገድ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ቤኛ፤ በአሁኑ ወቅት በምዕራብ ኦሮሚያና መካከለኛው ኦሮሚያ አካባቢ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊዘንብ ስለሚችል ተገቢው ጥንቃቄ እንዲደረግ አስገንዝበዋል።
በታሪክ አዱኛ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!