የከተማ አስተዳደሩ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ላልነበራቸው ነባር የመስጊድ ይዞታዎች 70 የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ አስረከበ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የመስጂድ እና የምርምር ማእከል የግንባታ ቦታ ርክክብ ተካሄደ።
የከተማ አስተዳደሩ ለመስጅዱ ግንባታ የሚያገልግል 30 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታንም አስረክቧል ።
ኢ/ር ታከለ ኡማ ቦታውን ለኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር እድሪስና ለአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼኽ ሱልጣን አማን አስረክበዋል።
ኢ/ር ታከለ ይህ የዓለም አቀፍ መስጂድ የግንባታ ቦታ ለሙስሊሙ ማህበረሰብ የተሰጠ የኢድ በዓል ስጦታ መሆኑን ተናግረዋል።
ቦታው የመንግስት ይዞታ እንደነበር ያነሱት ኢንጂነር ታከለ፥ ከዚህ ቀደም ከመንግስት ተቋም እንደተነጠቀው ሁሉ አሁንም በፍጥነት ወደ ግንባታ ሳይገባ ተቀርቶ ይህ እንዳይሆን ሙስሊሙ ማህበረሰብ በቦታው ላይ በፍጥነት ግንባታውን እንዲጀመር አሳስበዋል።
የከተማ አስተዳደሩም ግንባታው እውን እንዲሆን ድጋፉን እንደሚያደርግ ነው ያረጋገጡት።
ከቀናት በኋላ የሚከበረውን የኢድ አልፈጥር በዓልም በመረዳዳት እና እርስ በእርስ በመደጋገፍ ማክበር እንደሚገባ የተናገሩት ኢ/ር ታከለ ኡማ፥ ለበዓሉ የመልካም ምኞት መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል።
የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ላልነበራቸው ነባር የመስጂድ ይዞታዎችም 70 የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ አስረክበዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር እድሪስ ለሙስሊሙ ማህበረሰብ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼኽ ሱልጣን አማን በበኩላቸው የዛሬው ሁነት ሙስሊሙ ማህበረሰብ ሲያነሳቸው ለነበሩ ጥያቄዎች ምላሽ የተሰጠበት መሆኑን ነው የጠቆሙት።
ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አስተያየታቸውን የሰጡ በስነ ሰርዓቱ ላይ የተገኙ የእምነቱ ተከታዮች በአፍሪካ ህብረት አቅራቢያ የሚገነባው ይህ መስጂድ ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡም ከፍተኛ ግልጋሎት እንደሚሰጥ እምነታቸው መሆኑን ገልፀዋል።
በጥበበስላሴ ጀምበሩ
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዘናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።