Fana: At a Speed of Life!

የጥጥ ምርታማነት ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች እንዳሉበት ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የጥጥ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች እንደተደቀኑበት ተጠቆመ።

የዓለም የጥጥ ቀን “የጥጥ ልማት ለተፋጠነ የግብርና መዋቅራዊ ሽግግር” በሚል መሪ ሃሳብ በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አሚባራ ወረዳ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ለሁለተኛ ጊዜ ተከብሯል።

በዕለቱም ከጥጥ ምርት ጋር በተያያዘ ግንኙነት ያላቸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ተወካዮች፣ የጨርቃጨርቅ አምራች ፋብሪካዎች እና የጥጥ ዕሴት ሰንሰለት ባለድርሻዎች ተሳትፈዋል።

ዕለቱን በአፋር ክልል አሚባራ ወረዳ ወረር ቀበሌ የጥጥ ሰብል አምራች አርሶአደሮች እና አልሚዎችን እርሻ አሁናዊ ቁመና በመጎብኘት እንዲሁም ወረር የግብርና ምርምር ማዕከል ዘርፉን ለማሸጋገር እየሰራ ያለውን ሥራ በመመልከት የዘርፉ ተዋናዮች አክብረውታል።

በመርሐግብሩ ላይ በግብርና ሚኒስቴር የጥጥ ልማት መሪ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሳምሶን አሰፋ እንደገለጹት፥ የጥጥ ምርታማነትን ለማሳደግ የተለያየ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

ቀኑ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ መከበሩ የጥጥ ምርት ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ያለውን ድርሻ ለማሳወቅ፣ በዘርፉ ያሉ ችግሮችን የጋራ አድርጎ እልባት ለመስጠትና መልካም ዕድሎች ለመመልከት በማሰብ መሆኑ ተነግሯል።

በተለይም ዘርፉ በየዓመቱ በሌሎች የሰብል አይነቶች ሽሚያ ያለበት መሆኑ፣ የገበያ ትስስር ችግር፣ የምርት ጥራት፣ በቴክኖሎጂ ክፍተት እና የተሻሻለ ዘር ዕጥረት ለጥጥ ምርታማነት እንቅፋት መሆኑ ተመላክቷል።

በኢትዮጵያ ያሉ የጨርቃጨርቅ አምራች ኢንዱስትሪዎች በዓመት 106 ሺህ ቶን የተዳመጠ የጥጥ ምርት የሚፈልጉ ቢሆንም አሁን ላይ በሀገር ውስጥ ምርት ብቻ ይህን መሸፈን አልተቻለም ነው የተባለው።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም የጥጥ ሰብል ምርትን በባለቤትነት ከወሰደበት ጊዜ ጀምሮ አሁናዊ የጥጥ ምርት ተግዳራቶችን ለመፍታት፣ በራስ ዓቅም የሀገር ውስጥ ፍጆታን ለመሸፈን እና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ዋና መሪ ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።

በመራኦል ከድር

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.