ኬንያ አፍሪካውያን ያለ ቪዛ ወደ ግዛቷ እንዲገቡ ልትፈቅድ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኬንያ አፍሪካውያን ያለ ቪዛ በግዛቷ መንቀሳቀስ እንዲችሉ ልትፈቅድ መሆኑን የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ገለፁ፡፡
ፕሬዚዳንቱ ይህን ያሉት በኮንጎ ብራዛቪል በተካሄደው የሶስቱ ተፋሰስ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው፡፡
በንግግራቸው ኬንያ ይህን የወሰነችው ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን የንግድ ልውውጥ ለማሳደግ በማለም መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ቀደም ሲል በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የቪዛ መስፈርት እና ታሪፍ በመሰረዙ የንግድ ልውውጡ በከፍተኛ ደረጃ ማደጉን አመላክተዋል።
በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ስምምነት ላይ የተደረሰበት የአፍሪካ አህጉራዊ የነጻ ንግድ ቀጠና ተግባራዊ እንዲሆን በአፍሪካ አህጉር ያለው ያለው የጉምሩክ ታሪፍ እንዲቀንስም አስገንዝበዋል፡፡
በ2024 ወደ ኬንያ ለመጓዝ የሚያስቡ አፍሪካውያን ዜጎች ቪዛ አያስፈልጋቸውም ማለታቸውን ክላይሜት ቼንጅ መፅሄት አስነብቧል፡፡