በኮንታ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ የሶስት ሰዎች ህይወት አለፈ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኮንታ ዞን አመያ ዙሪያ ወረዳ በተፈጠረ የመሬት መንሸራተት አደጋ የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉን የዞኑ ኮሙኒኬሽን ገለፀ፡፡
በወረዳው ኦፓላሸ ቀበሌ በግምት ከምሽቱ 9 ሰዓት አካባቢ በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ የሶስት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 25 አባዎራዎችና 175 የቤተሰብ አባላት ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው ተገልጿል፡፡
ሟቾቹ የአንድ ቤተሰብ አባላት መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡
በተጨማሪም በአደጋው የቤት እንስሳት ሲሞቱ በ5 ነጥብ 5 ሄክታር ማሳ ላይ የነበረ ሰብልም ወድሟል ነው የተባለው፡፡
የመሬት መንሸራተት አደጋው በዞኑ የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ የተከሰተ መሆኑን ከኮንታ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡