በአማራ ክልል በያዝነው ዓመት 250 ሺህ ሔክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ እንደሚለማ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተያዘው ዓመት 250 ሺህ ሔክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ እንደሚለማ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
የ2016 ክልላዊ የበጋ መስኖ ስንዴ ንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሐ -ግብር በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ደዋ ጨፋ ወረዳ ተካሂዷል፡፡
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) በንቅናቄው ማስጀመሪያ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ክልሉ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ቢሆንም ምርታማነትን ለማሣደግ በቁርጠኝነት እየተሠራ ነው ብለዋል።
በተያዘው ዓመት ከ333 ሺህ ሔክታር መሬት በላይ በመስኖ እንደሚለማና ከዚህ ውስጥ 250 ሺህ ሔክታሩ በስንዴ እንደሚሸፈን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳኅሉ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ ከመስኖ ልማት 9 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይጠበቃል ማለታቸውን የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ኮሙኒኬሽን መምሪያ መረጃ አመላክቷል፡፡
ንቅናቄው በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች እንደሚተገበር ጠቁመው÷ በሚቀጥሉት ወራት ሰፊ የመስኖ ሥራ የሚከናወንበት ወቅት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በዝናብ እጥረትና ሌሎች ምክንያቶች ያጣነውን ምርት ሊያካክስ በሚችል መልኩ የተሻለ ምርት ለማግኘት እንሠራለን ነው ያሉት፡፡