Fana: At a Speed of Life!

በቀጣዮቹ አስር ቀናት አንዳንድ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖራቸው ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀጣዮቹ አስር ቀናት አንዳንድ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖራቸው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጠው ማብራሪያ÷ በመደበኛ ሁኔታ በቀጣዮቹ አስር ቀናት በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የበጋው ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ የሚያመዝን መሆኑን አንስቷል፡፡

በተጨማሪም በደቡብ ምዕራብ፣ በደቡብና በደቡብ ምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር አመልክቷል፡፡

በሚቀጥሉት አስር ቀናት በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት በደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ለዝናብ መኖር አመቺ ሁኔታ የሚፈጥሩ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተጠቅሷል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብና በምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የተሻለ ገጽታ እንደሚኖራቸው አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በደቡብ ምዕራብና በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተስፋፋና ሰፊ ቦታዎችን የሚያካትት ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ይኖራቸዋል ተብሏል ፡፡

በሌላ በኩል በመካከለኛው፣ በምስራቅ እና በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ከሚጠናከሩት የአየር ሁኔታ ክስተቶች ላይ በመነሳት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንደሚኖር ተጠቁሟል፡፡

በአጠቃላይ በሚቀጥሉት አስር ቀናት ከኦሮሚያ ክልል ሁሉም የወለጋ ዞኖች፣ ጅማ፣ ኢሉባቦር፣ ቡኖ በደሌ፣ ሁሉም የአርሲ፣ የባሌና የጉጂ ዞኖች፣ ምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ፣ የቦረና ዞን፤ ከአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም፣ መካከለኛው፣ ሁሉም የጎንደር ዞኖች፣ የባህር ዳር ዙሪያ እና አዊ ዞን ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖራቸው ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም የቤንሻንጉል ክልል ዞኖች፤ የሲዳማ ክልል ዞኖች፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፤ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፤ የሱማሌ ክልል ዞኖች እንዲሁም ሐረሪ እና ድሬዳዋ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይኖራቸዋል፡፡

በጥቂት ስፍራዎቻቸው ላይ ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖርም ኢንስቲትዩት አሳስቧል፡፡

የጋምቤላ ክልል ዞኖች፣ የመካከለኛው ኢትዮጵያ ክልል፣ የሰሜን እና የደቡብ ወሎ ዞኖች፣ ምሥራቅ ጎጃም፣ አዲስ አበባ፣ ሁሉም የሸዋ ዞኖች፣ የምዕራብ፣ የሰሜን ምዕራብና የደቡብ ትግራይ ዞኖች እንዲሁም ከአፋር ክልል ዞን 3፣ 5 እና 1 በአንዳንድ ሥፍራዎቻቸው ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንደሚያገኙም የትንበያ መረጃዎች አመላክተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.