Fana: At a Speed of Life!

ሀሰተኛ የውጭ ሀገራት ገንዘቦችን በማተም ወንጀል የተጠረጠሩ የውጭ ሀገር ዜጎች ላይ ክስ ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዘንዶ ቆዳ እና የተፈጥሮ ማዕድን በመያዝ እንዲሁም ሀሰተኛ የውጭ ሀገራት ገንዘቦችን በማተም ወንጀል የተጠረጠሩ የውጭ ሀገር ዜጎች ላይ ክስ ተመሰረተ።

ክሱ የተመሰረተው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ልደታ ምድብ 14ኛ ልዩ ልዩ ወንጀል ችሎት ሲሆን÷የፍትሕ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ ተደራራቢ ክሶችን አቅርቦባቸዋል።

ክስ የቀረበባቸው ተከሳሾችም 1ኛ አቦየም መኮምቢሊ ጂ፣ 2ኛ ርሆቦት ሮሄ ፣ 3ኛ ዳውድ ሲዲኪእና ኪምቢ ኪምቢ ጆን ይባላሉ።

በተከሳሾቹ ላይ የቀረበው አንደኛው ክስ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) እና አንቀጽ 356 ላይ የተደነገገውን ድንጋጌ ተላልፈዋል በሚል ነው።

ተከሳሾቹ ተከራይተው በሚኖሩበት በአዲስ አበባ ለሚ ኩራ ክ/ከተማ ወረዳ 09 ልዩ ቦታው ቦሌ አዲስ ት/ቤት አካባቢ ነሐሴ 3 ቀን 2015 ዓ.ም በፀጥታ አካላት በተደረገ ክትትል በጋራ በመሆን ሀሰተኛ ገንዘብ ለመስራት የሚያገለግሉ መሳሪያዎች፣ የተለያዩ ኬሚካሎች እና ሀሰተኛ ገንዘብ መስሪያ ወረቀቶችን በመጠቀም ሀሰተኛ የውጭ ሀገራት ገንዘቦች አመሳስለው በመስራት ላይ እያሉ እጅ ከፍንጅ መያዛቸው በክሱ ተመላክቷል፡፡

በዚህም ዐቃቤ ሕግ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተሳታፊ በመሆን ሀሰተኛ ገንዘብ የመስራት ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።

በ2ኛው ክስ ላይ ደግሞ ተከሳሾቹ አንድ የብር ማተሚያ ማሽን ፣ ሀሰተኛ ገንዘብ ለመስራት የሚጠቀሙባቸው የተለያዩ ኬሚካሎች ፣ በዶላር ቅርፅ የተቆረጠ 55 ወረቀት፣ ጥቁር በዶላር ቅርፅ የተቆረጠ 27 ወረቀት፣ የሀሰት ገንዘብ ማዘጋጃ ኦሬንጅ ወረቀት እና ሌሎች 109 ወረቀት እንዲሁም22 የዶላር ማሸጊያ ፕላስቲክና ዶላር ለማተም የሚያገለግሉ መሳሪያዎች ተከሳሾቹ በጋራ ሲጠቀሙባቸው መገኘታቸው ተጠቅሷል፡፡

በዚህም ዐቃቤ ሕግ ሀሰተኛ ነገሮችን ለመስራት የሚያገለግሉ መስሪያ እና መሳሪያዎች መያዝ ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል፡፡

በተጨማሪም ተከሳሾቹ በጋራ በመሆን ምንም አይነት ፈቃድ ሳይኖራቸው 71 ነጥብ 15 ግራም የሚመዝን ካኦሊናይት የተፈጥሮ ማዕድን በመኖሪያ ቤት ውስጥ ይዘው የተገኙ መሆኑን የጠቀሰው ዐቃቤ ሕግ÷ ፈቃድ ሳይኖረው የተፈጥሮ ማዕድን መያዝ እና የአዋጁን ድንጋጌዎች መተላለፍ ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል፡፡

በሌላ በኩል በሁሉም ተከሳሾች ላይ በተደረገው ማጣራት የፀና የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸው በሀገር ውስጥ ሲኖሩ የተያዙ መሆናቸው በክሱ ተገልጾ÷ የፀና የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖር በሀገር ውስጥ የመኖር ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።

በተጨማሪም ፈቃድ ሳይኖራቸው የዱር እንስሳት ቆዳ ማለትም የዘንዶ ቆዳ ይዘው የተገኙ በመሆኑ በፈፀሙት ምንም አይነት ፈቃድ ሳይኖር የዱር እንስሳት ውጤቶች ይዞ መገኘት ወንጀል ክስ ተከሰዋል።

በተጨማሪም ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች በተጠቀሰው ተከራይተው ይኖሩበት በነበረው መኖሪያቸው ውስጥ አጠቃላይ 2 ሺህ 705 ሀሰተኛ የአሜሪካ ዶላር የተገኘ በመሆኑ÷ ሀሰተኛ ገንዘብ ይዞ የመገኘት ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።

አራተኛ ተከሳሽ በአራተኛ ክስ ላይ ብቻ የተጠቀሰ ሲሆን÷ ቀሪዎቹ ግን በሁሉም ክሶች ላይ መካተታቸው ተመላክቷል፡፡

በዚህ መልኩ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበባቸው ተደራራቢ ክሶች በችሎት እንዲደርሳቸው የተደረገ ሲሆን÷ ተከሳሾቹ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል።

ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ ላይ የቀረበው ተደራራቢ ክስ መሆኑን እና የተፈጸመው ወንጀል የሀገር ኢኮኖሚን የሚጓዳ ተግባር መሆኑን ጠቅሶ÷ የዋስትና ጥያቄያቸውን በመቃወም ተከራክሯል።

በተጨማሪም ተከሳሾቹ ቋሚ አድራሻና የፀና የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው በመሆኑ በዋስ ቢወጡ የዋስትና ግዴታቸውን አክብረው ላይቀርቡ ይችላሉ በማለት የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ እንዲደረግ ጠይቋል።

የግራ ቀኙን ክርክር የተከታተለው ችሎቱ መርምሮ ዋስትናው ላይ ብይን ለመስጠት ለፊታችን ጥቅምት 26 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.