Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ ሰው ተኮር ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ – አቶ ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በክልሉ የሕዝብን ችግር ለመቅረፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ፡፡

የሐረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ሲያካሂደው የቆየው የ2016 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ተጠናቋል።

በግምገማው ላይ ርዕሰ መሥተዳድሩ÷ በጳጉሜ ወር የተከናወኑት  ሰው ተኮር ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በየዘርፉ ማነቆዎችን በመለየት ከመፍታት አንጻር ውስንነቶች እንደሚስተዋሉ የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ÷ ከተለመዱ አሠራሮች ያለመውጣት ክፍተቶችም በቀጣይ እንዲታረሙ አሳስበዋል።

በተለይ ሠላምና የሕግ የበላይነትን ለማጠናከር÷ የሠላም ዕሴት የግንባታ ሥራዎች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

የተጀመሩ የመንገድ፣ የውሃ፣ የመስኖ እና ሌሎች ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ የማድረግ እንዲሁም ሥራ ያልጀመሩ ፕሮጀክቶች በአፋጣኝ እንዲጀመሩ አመራሩ በቁርጠኝነት እንዲሠራም አሳስበዋል።

የሥራ ዕድል ፈጠራን የሁሉም ተቋማት ማድረግና ሕዝቡን እያማረረ የሚገኘውን “የኑሮ ውድነት” ለማቃለል ልዩ ትኩረት ሰጥቶት መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለመጨረስ፣ የትምህርት ጥራትን ለማጎልበት፣ የቱሪዝም ዘርፉን ለማጠናከር እንዲሁም የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመቅረፍም ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ዓመት በሐረር ከተማ የሚከበረው 26ኛው የሐረሪ የባሕልና ስፖርት ፌስቲቫል በተሳካ ሁኔታ እንዲከበር በትጋት መሥራትያስፈልጋል መለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.