ለሁሉም ምቹ የሆነች ሀገርን ለመፍጠር የሚያስችል የሪፎርም ሥራ እየተሠራ መሆኑን አቶ አደም ፋራህ ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሁሉም ምቹ የሆነች ሀገርን ለመፍጠር የሚያስችል የሪፎርም ሥራ እየተሠራ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።
የሪፎርም መሰረታውያንና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሚና በሚል ርዕስ በአፍሪካ አመራር ልኅቀት አካዳሚ ሥልጠና ተሰጥቷል።
መንግሥት ለሀገርና ለዜጎች ደኅንነት መጠበቅ ኃላፊነት የተጣለበት በመሆኑ ሁሉንም ዜጋ ያካተተ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት የሚያስችሉ የሪፎርም ሥራዎች መከናወናቸውን አቶ አደም ፋራህ በስልጠናው ላይ ተናግረዋል።
ሁሉን አካታች የሆነ፣ እውነተኛ ኅብረ- ብሄራዊ የፌዴራል ሥርዓትን ለመገንባት እየተሠራ ነው ማለታቸውን ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
በተጨማሪም ለሁሉም ምቹ የሆነች ሀገርን ለመፍጠር የሚያስችል አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማሕበረሰብን በመገንባት የሪፎርም ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የሪፎርሙ ዓላማም ሀገሪቱ ከገባችበት አለመረጋጋትና ሥጋት መታደግና ኢኮኖሚውን በማሻሻል የሕዝቡን ኑሮ መለወጥ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በኢኮኖሚ የግሉን ዘርፍ የማሳተፍ፣ ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ፣ ተወዳዳሪነትንና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ሥራ እንደሚሠራም አመላክተዋል፡፡