አሜሪካ በጋዛ ተኩስ አቁም እንዲደረስ የማትፈቅድ ከሆነ ዋጋ ትከፍላለች – ኢራን
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ በጋዛ ተኩስ አቁም እንዲደረስ የማትፈቅድ ከሆነ ዋጋ ትከፍላለች ስትል ኢራን አስጠነቀቀች፡፡
ቴህራን ዋሺንግተን በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ግጭት እንዲባባስ እያደረገች ነው ስትል ከሳለች።
የኢራኑ መካለከያ ሚኒስትር ሞሃመድ ሬዛ አሺቲያኒ፥ ለአሜሪካ ያለን ምክር ጦርነቱን እንድታስቆም እና በጋዛ ተኩስ አቁም እንዲደረስ ግፊት እንድታደርግ ነው ብለዋል።
ይህ የማይሆን ከሆነ ግን አሜሪካ አስከፊ መዘዝ ይጠብቃታል ያሉት ሚኒስትሩ ÷ በጋዛ እየተካሄደ ያለው ደም አፋሳሽ ጦርነት እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡
በጋዛ ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከባግዳድ ድንገተኛ ጉብኝት በኋላ ቱርክ መግባታቸው ተሰምቷል፡፡
ብሊንከን በአንካራ ቆይታቸው ከቱርኩ ፕሬዚዳንት ረጂፕ ጣይፕ ኤርዶኻን ጋር በወቅታዊው የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በእስራኤል እና ሃማስ መካከል ሀይለኛ ውጊያ እየተካሄደ ሲሆን እስራዔል የአየር ጥቃቷን አጠናክራ በመቀጠል 450 ኢላማዎችን መትቻለሁ ብላለች፡፡
የእስራኤል ጦር እንዳስታወቀው የእግረኛ ጦሩ በጋዛ ደቡባዊ አቅጣጫ የሚገኘውን የባህር ጠረፍ የተቆጣጠረ ሲሆን፥ አካባቢውን ለሁለት በመቁረጥ የምድር ላይ ዘመቻውን እያካሄደ ነው ማለቱን ቢቢሲ እና አር ቲ ዘግበዋል፡፡
አሜሪካ ከቀናት በፊት በእስራኤል ሃማስ ጦርነት ‘ሙሉ የተኩስ አቁም’ ከሚደረስ ይልቅ ‘ሰብአዊ የተኩስ አቁም’ ቢደረስ እመርጣለሁ ማለቷ ይታወሳል።
ዋሺንግተን ቴል አቪቭ ራሷን የመከላከል መብት አላት በሚል በጋዛ እየወሰደች ላለው ወታደራዊ እርምጃ ድጋፏን የገለጸች ሲሆን፥ በአንጻሩ ኢራንን ጨምሮ የባህረ ሰላጤው ሀገራት እስራኤል በአሜሪካ ድጋፍ ‘የጦር ወንጀል እየፈጸመች ነው’ በማለት ይከሳሉ።
ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ የፖለቲካ ተንታኞች ደግሞ የእስራኤል ሃማስ ጦርነት ቀጠናውን ወደ ለየለት ቀውስና ግጭት እንዳይከተው ስጋታቸውን ይገልጻሉ።