ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን ጸድቆ በራሱ እስኪቆም መንከባከብ አስፈላጊ ነው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን ጸድቆ በራሱ እስኪቆም ድረስ በዘላቂነት መንከባከብ አስፈላጊ ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷የአካባቢ ጥበቃ ከክልሉ ዘጠኝ የግብርና የትኩረት አቅጣጫዎች አንዱ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በዚህ ረገድ የአፈርና ውሃ ጥበቃ እንዲሁም የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎች በተሻለ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኙ ነው የገለጹት፡
ከጥቂት ወራት በፊት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ጉራዋ ወረዳ የተተከሉ ችግኞች አሁን ላይ በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የአካባቢው ሕብረተሰብ ለተተከሉት ችግኞች ላደረገው ተገቢ እንክብካቤም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን ፀድቆ በራሱ እስኪቆም ድረስ በዘላቂነት መንከባከብ አስፈላጊ ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡