በክልሉ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሙሉ በሙሉ እና በከፊል የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ የክልሉ ርዕሰ መስተሰዳደር አሻድሊ ሃሰን ጥሪ አቀረቡ፡፡
አቶ አሻድሊ ሀሰን፣ የተጎዱ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት ከተቋቋመው ክልላዊ የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ ጋር የተወያዩ ሲሆን፣ ለኮሚቴውም አቅጣጫ ሰጥተዋል።
በዚህ ወቅት ርዕሰ መስተዳደሩ ÷በክልሉ ባለፉት ዓመታት በጸጥታ ችግር ሙሉ በሙሉ እና በከፊል የወደሙ ተቋማትን በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ገቢ በማሰባሰብ ወደነበሩበት ለመመለስ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ሙሉ በሙሉም ሆነ በከፊል የወደሙ ትምህርት ቤቶችን ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ መልሶ-በመገንባት ምቹ የትምህርት ቤት አካባቢ መፍጠር እንደሚገባ ገልጸዋል።
በክልሉ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በፈጠሩት የጸጥታ ችግሮች 164 የ1ኛ ደረጃ እና 10 የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ እንዲሁም፣ 91 የ1ኛ 18 የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በከፊል መውደማቸው ተገልጿል።
ለትምህርት ተቋማት መልሶ-ግንባታ የሚያስፈልገውን 3 ቢሊዮን 683 ሚሊዮን ብር ከባለድርሻ አካላት ለማሰባሰብ መታቀዱን የገለፁት ርዕሰ መስተዳደሩ÷ ሁሉም ባለደርሻ አካል የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
በተጨማሪም ገቢ አሰባሰቡን በበላይነት የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደሥራ የገባ ሲሆን፣ በቀጣይም ዝግ የባንክ አካውንት በመክፈት እና በአጭር የጽሁፍ መልዕክት ገቢ ለማሰባሰብ ዝግጅት እየተደረገ ነው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡