እስራኤል ጋዛን በወታደራዊ ኃይል ማስተዳደር የለባትም ስትል አሜሪካ አስጠነቀቀች
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እስራኤል ጋዛን ለረጅም ጊዜ ተቆጣጥሮ መቆየት የለባትም ስትል አሜሪካ አስጠነቀቀች፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ፥ የእስራኤል ወታደራዊ ሀይሎች ጋዛን ከመቆጣጠር ባለፈ የተራዘመ ወታደራዊ ሃላፊነታቸውን ይወጣሉ ብለዋል።
ይህን ተከትሎም አሜሪካ እስራኤል ጋዛን “መልሶ መቆጣጠርና” ለረጅም ጊዜ ተቆጣጥሮ መቆየቱ አደጋ አለው ስትል አስጠንቅቃለች።
የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ÷ እስራኤል በጋዛ የእግረኛ ጦሯን በማስፈር እና ጋዛን በድጋሚ በመቆጣጠር ለረጅም ጊዜ በወታደራዊ ኃይል ለማስተዳደር ያቀደችውን እቅድ እንደገና እንድታጤነው አስጠንቅቀዋል።
ጋዛን በወታደራዊ ኃይል ማስተዳደር ለእስራኤል መንግስትም ሆነ ለህዝቦቿ የሚጠቅም አይደለም ነው ያሉት ቃል አቀባዩ።
ከእስራኤል ወታደራዊ ኃይል ባለፈ የጋዛ ሰርጥን ማን ያስተዳድረው በሚለው ጉዳይ አስተያይት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
የእስራኤል ጦር ጋዛን ያስተዳድራል የሚለው የኔታንያሁ ሃሳብ ግን ከእስራኤሉ መከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት ተቃውሞ ገጥሞታል።
መከላከያ ሚኒስትሩ የእስራኤል ጦር የታሰበውን ወታደራዊ ዘመቻ መፈጸም እንጅ ‘የጋዛን የቀን ተቀን እንቅስቃሴን’ በተመለከተ ሃላፊነት የለበትም ብለዋል።
አሜሪካ ለእስራኤል ወታደራዊ ድጋፎችን ስታደርግ የቆየች ቢሆንም የእስራኤል ወታደራዊ ኃይል በጋዛ ለረጅም ጊዜ እንዲሰማራ ግን ፈቃድ አለመስጠቷን አር ቲ ዘግቧል፡፡