ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ከኔዘርላንድስ አምባሳደር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በኔዘርላንድስ አምባሳደር ሄን ጃን ባከር ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ÷የክልሉ መንግስት እየተገበረ ያለውን የልማት አቅጣጫ በአምባሳደሩ ለተመራው ልዑክ ገለጻ አድርገዋል፡፡
በክልሉ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በተመለከተም ለልዑካኑ ያብራሩ ሲሆን፥ ከኔዘርላንድስ ለሚመጡ ባለሀብቶች የክልሉ መንግስት እያደረገ ያለውን ድጋፍ ያጠናክራል ብለዋል።
የክልሉ መንግስት በእንስሳት እርባታና የዝርያ ማሻሻያ ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡
የኔዘርላንድስ መንግስት በእንስሳት እርባታ ያለውን ልምድ እንዲሁም የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን በሚመለከት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
አምባሳደር ሄን ጃን ባከር በበኩላቸው፥ የኔዘርላንድስ መንግስት በኔዘርላንድ የልማት ድርጅት በኩል የአርሶአደሩን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ዘላቂ “የኃይል የሙከራ” ስራ አስጀምሮ እየሰራ ነው ማለታቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
አምባሳደሩ የክልሉ መንግስት ለኔዘርላንድስ ባለሀብቶች በክልሉ ለሚያፈሱት መዋዕለ ንዋይ እያደረገ ስላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በወተትና በዶሮ እርባታ ዙሪያ በክልሉ ዘጠኝ ወረዳዎችና ሁለት ከተማ መስተዳድሮች ውስጥ እየሰራ ነውም ተብሏል፡፡