አዲስ አበባን ተወዳዳሪና ተመራጭ ከተማ የማድረግ ራዕያችንን እናሳካለን – አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ አበባን ተወዳዳሪና ተመራጭ ከተማ የማድረግ ራዕያችንን እናሳካለን ሲሉ የኢዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባዋ በሞሮኮ ማራካሽ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ፎረም የአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎች መድረክ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
ከንቲባዋ በፎረሙ በከተሞች አጠቃላይ ዕድገት ዕድሎች እና ተግዳሮቶች እንዲሁም ለፈጣን የከተሞች ዕድገት አቅም የሚሆን የፋይናንስ ምንጭን በተመለከተ ውይይት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች በመድረኩ የአዲስ አበባን የልማት ፍኖት፣ የፋይናንስ ስርዓት እና የገቢ አሰባሰብ ልምድን ማካፈላቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
በመድረኩ የአፍሪካ ልማት ባንክ ለከተሞች ልማት የሚውል የ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር የድጋፍና ብድር አቅርቦት አፅድቋል ያሉት ከንቲባዋ÷ከድጋፉ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችሉ መሰረታዊ የልማት ፕሮጀክቶችን በማቅርብ አዎንታዊ ምላሽ አገኝተናል ብለዋል።
አዲስ አበባ በፈጣን ለውጥ ውስጥ የምትገኝ ፣ የተረጋጋችና ሰላማዊ በመሆኗ በመርሐ-ግብሩ የተሳተፉ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ተቋማት በበከተማዋ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጋብዘዋል፡፡
ሁሉንም የልማት ዕድሎች እና አቅሞ በማስተባበር አዲስ አበባን ተወዳዳሪና ተመራጭ ከተማ የማድረግ ራዕያችንን እናሳካለን ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡