ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የሳዑዲ አፍሪካን ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገለጹ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 30 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የሳዑዲ አፍሪካን ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሳዑዲ አፍሪካ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፥ ለበርካታ አስርት አመታት ሳዑዲ ለአፍሪካ ዕድገት ያሳየችውን ቁርጠኝነት አንስተዋል።
በዚህም በሳዑዲ የልማት ፈንድ እና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት አማካኝነት ለአፍሪካ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋፅዖ ማበርከቱን ገልጸዋል።
አያይዘውም በመሰረተ ልማት፣ ታዳሽ ሃይል፣ ግብርና፣ ጤና እና ትምህርት ላይ ፈሰስ በማድረግ ለአፍሪካ ዕድገት የሚደረገው ጥረት አበረታች መሆኑንም ጠቁመዋል።
አፍሪካ አሁን ላይ ለአህጉራዊ ውህደት መሰረት መጣሏን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ኢኮኖሚያዊ ነጻነቷን ለማረጋገጥም አስደናቂ እመርታ ማሳየቷን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ለሁለቱ ሀገራት የጋራ እድገት እና ለሳዑዲ አፍሪካ ትብብር መጠናከር ከሳዑዲ ጋር በቅርበት ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗንም አስረድተዋል።
ዓለምአቀፉ የአቅርቦት ሰንሰለት መስተጓጎል በአፍሪካ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ማሳደሩ አያጠራጥርም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የምግብ ዋስትና እና የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ከመቸውም ጊዜ በላይ አስፈላጊው አጀንዳ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው የግብርናው ዘርፍ ለኢትዮጵያ ከአምስቱ ቁልፍ የልማት ምሶሶዎች አንዱ መሆኑን አንስተዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም በሀገር አቀፍ ደረጃ በስንዴ ልማት በአመት ሁለት ጊዜ ከ6 ሚሊየን ሄክታር በላይ በማልማት ምርት መጨመር መቻሉንም ነው የገለጹት።
ከዓመት በፊት በሀገር አቀፍ ደረጃ ‘በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር’ የዶሮ እርባታን ጨምሮ፥ የወተት፣ የከብት እርባታ እና የከተማ ግብርናን ለማበረታታት ትልቅ ስራ መጀመሩንም አውስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በንግግራቸው በአፍሪካ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ተጨማሪ ሀብት እና ካፒታል መመደብ እንዲሁም የሳዑዲ ኢንተርፕራይዞች በግብርናው፣ ኢንቨስትመንት እና በግብርና ማቀነባበር እንዲሁም በግብርና ቢዝነስ ፕሮግራሞች ላይ እንዲሳተፉ ማበረታታት የጋራ ተጠቃሚ ያደርጋልም ነው ያሉት።
ከአረንጓዴ ልማት ጋር በተያያዘ ባነሱት ሃሳብም ኢትዮጵያ ከፈረንጆቹ 2019 ጀምሮ የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ጋር በተያያዘ ተግባራዊ እርምጃ ስትወስድ መቆየቷን አስታውሰዋል።
በዚህም በዓመት ከ25 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ባሳተፈ ግዙፍ የደን ልማት ፕሮግራም ኢትዮጵያ 32 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞች መትከሏንም ነው ያስረዱት።