‘ሁዋዌ ሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር 2023’ የስልጠና መርሐ ግብር ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከጥቅምት 19 እስከ ጥቅምት 26 ቀን 2016ዓ.ም ከ14 ዩኒቨርሲቲዎች ለተውጣጡ 106 ተማሪዎች ስልጠና ሰጥቷል።
ዛሬ በተካሄደው የመዝጊያ ስነ-ስርዓት ላይ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስራ ፈጠራንና ክህሎት ማጎልበት ስራን መሃል ላይ ሆኖ ያስተባብራል ብለዋል፡፡
የዚህ ማሳያ የሚሆነው ሁዋዌን የመሳሰሉ ቴክኖሎጂን ይዘው የሚመጡ ከፍተኛ አበርክቶ ያላቸውን ዓለም አቀፍ ተቋማትን በመጋበዝና ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ስራ በአገራችን እንዲስፋፋ በማድረግ ነው ብለዋል።
አክለውም ሰልጣኞች የሰለጠኑበት የስልጠና ዘርፍ ከመንግስት የትኩረት ዘርፎች አንዱ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ተማሪዎቹ በስልጠናው የሰሯቸው ፕሮጀክቶች ውስጥ ያሉ የፈጠራ ሃሳቦች መሬት መንካት እንደሚኖርባቸውና መደገፍ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
አክለውም የግሉ ዘርፍ በሚሰራቸው ስራዎች ውስጥ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሚና ወደስራ በሚሰማሩበት ጊዜ የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች እንዲያልፉ መደገፍና ማገዝ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
በንግድ ሊሰማሩ፣ በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ዋነኛ ሞተር ሆነው ሊሰሩ፣ ሊያሰለጥኑ፣ በተፈጠረው ገበያም ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉበት እውቀት ግንዛቤና ክህሎት የተላበሱ በመሆኑ ከሁዋዌም ጋር ይሁን ከግለሰቦች ጋር እንደዚሁም ኢንተርፕራይዝ ወደፊት መስርተው ሲመጡ ተገቢ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ገልጸዋል።
በዚህ ሂደት ለተሳተፉ አካላት ምስጋና ማቅረባቸውን ከሁዋዌ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።