የአፍሪካ ኢኮኖሚ ጉባኤ በመዲናዋ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2023 የአፍሪካ ኢኮኖሚ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡
በጉባኤው ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴና የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበልን ጨምሮ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የኢንዱስትሪ ባለሙያዎች፣ የግሉ ዘርፍ ተወካዮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።
ጉባዔው ምሁራን እና ወጣት ተመራማሪዎች መፍትሄ ተኮር ምርምራቸውን ለፖሊሲ አውጪዎች እና ውሳኔ ሰጭዎች የሚያቀርቡበት እድል እንደሚፈጥርም ተገልጿል።
ጉባዔው በዋናነት በአፍሪካ ኢንዱስትሪ እድገት፣ ቁልፍ የኢኮኖሚ ደህንነት እና የዘላቂ ልማት አንቀሳቃሾች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ተብሏል፡፡
በታዳጊ ሀገራት የኢኮኖሚ ችግሮች እና እድሎች ላይ ምክክር እንደሚደረግበትም ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ፕሬዚደንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ፥ ጉባዔው የአፍሪካ 2063 አጀንዳን ለማሳካት ትርጉም ያለው አጋርነትን የሚያጎለብት እና መፍትሄዎችን የሚጠቁም ነው።
የኢንዱስትሪ ልማት ለሁሉን አቀፍ እድገት ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቅሰው ፥ በተለይ ዘርፉ የተለያዩ ጫናዎችንና ተጽእኖዎችን ተቋቁሞ መስራት እድገት ማስመዝገብ የሚችልበትን ስራ ማከናወን ይገባል ነው ያሉት፡፡
ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ብቻ ጥገኛ ከመሆን መላቀቅ የሚያስችሉ ስትራቴጂዎችን መንደፍ እንደሚገባም አመላክተዋል።
ለዚህ ደግሞ የአፍሪካ ሀገራት ብዝሃ ኢኮኖሚን መሰረት ያደረጉ ኢንዱስትሪዎችን በማስፋት ረገድ በትብብር መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ነው የጠቆሙት ፕሬዚደንቷ፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በበኩላቸው ፥ ጉባዔው የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ እና የኢንዱስትሪ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ መፍትሄዎችን የሚጠቁም መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም የኢንዱስትሪ ልማትን በማጎልበት ወደ ተግባር ለመቀየር የኢንዱስትሪ አቅምን ለማሳደግና ለማዘመን ልምድ የምንቀያየርበት ነው ብለዋል።
ጉባኤው የኢንዱስትሪ እድገትን በማፋጠን ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው ፥ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ በዘርፉ የምታከናውነው የሪፎርም ስራ በዘርፉ ያሉ ማነቆዎችን እያስወገደ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ከነበረበት 47 በመቶ ወደ 55 በመቶ ማሳደግ ተችሏልም ነው ያሉት፡፡
ጉባዔው በአፍሪካ ልማት ባንክ፣ በመንግስታቱ ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እና በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም በጋራ የተዘጋጀ ሲሆን÷ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት እንደሚቆይ ተገልጿል።